Home

Advertisement

125 LOGO125 years of Service

                                                              

 

we deliver small

ፖስታ ዜናዎች

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተመሰረተበትን 125ኛ ዓመት ዘንድሮ ያከብራል፡፡

     የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ1886 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ በህግ የተቋቋመ ሲሆን፣ አላማውን የፖስታ አገልግሎት ለመስጠት አድርጐ የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ የፖስታ ስራ በህግ ከመቋቋሙ በፊት የመልዕክት ማመላለስ ስራ ይሰራ የነበረው የቤተመንግስት መልዕክተኞች የመንግስትን ሰነዶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ

 

በሚያመላልሱበት ወቅት 125 LOGOእንደነበር መረጃዎች ያሣያሉ፡፡

      ከ1886 ዓ.ም  ጀምሮ ፖስታዎች ይመላለሱ የነበሩት መልዕክተኞች ወይም ፖስተኞች ተብለው በሚታወቁ ሰዎች ነበር፡፡  ፖስተኞቹ አስቸጋሪ መልክአ ምድሮችንና የአየር ጠባዮችን በመጓዝ ደብዳቤዎችን ያደርሱ ነበር፡፡

     መልዕክታቸውን በስንጥቅ ዘንግ አጣብቀው የመልዕክቱ ደህንነት ተጠብቆ እንዲደርስ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡  በጊዜው በአህያ፣ በበቅሎ እና በሌሎችም የጋማ ከብቶች በመታገዝ ስራቸውን በአግባቡ ይወጡ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

     ድርጅቱ ስራውን ሲጀምር የመጀመሪያዎቹን የአገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች የከፈተው በሐረር እና በእንጦጦ ነበር፡፡

     የጅቡቲ አዲስ አበባ የባቡር መስመር ስራ መጀመሩም የፖስታው እንቅስቃሴ ፍጥነት እንዲያገኝ እረድቶታል፡፡  ድርጅቱ አገልግሎቱን  ለማስፋፋት  የዓለም ፖስታ ህብረት አባል በ1901 ዓ.ም በመሆኑ አለም አቀፍ መልዕክት መላክ እንዲጀመር ረድቷል፡፡

     በ1886 ዓ.ም የታተሙት የመጀመሪያዎቹ ቴምብሮችም በአለም አቀፍ ደረጃ ድርጅቱ የህብረቱ አባል ከሆነ በኋላ መሰራጨት ጀምረዋል፡፡

    ድርጅቱ በ1973 ዓ.ም በተመሰረተው የመላው አፍሪካ ፖስታ ህብረት አባል በመሆንም አለም አቀፍ ተሣታፊነቱን አጠናክሯል፡፡

     በ1945 ዓ.ም የፖስታ አገልግሎት ከቴሌኮሙኒኬሽን ተለይቶ ራሱን ችሎ ተቋቁሟል፡፡  በ1958 ዓ.ም የፖስታ ማቋቋሚያ አዋጅ በመውጣቱም  የድርጅቱ ስራዎች በጉልህ ተለይተው እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡ 

    በ1981 ዓ.ም እየተስፋፋ የመጣውን የፈጣን መልዕክት ስራ ለመቋቋምም የፈጣን መልዕክት ስራ በኢትዮጵያ ተጀምሯል፡፡

     ድርጅቱ በተለይ መሰረታዊ አሰራር ሂደት ለውጥ ጥናትን ተግባራዊ ካደረገ በኋላ በርካታ አዳዲስ ስራዎችን የመስራት እና ነባር አገልግሎቶችን ደግሞ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡  የውክልና ስራዎች መስፋፋት፣ የፖስትባስ መጀመር፣ የቤት ለቤት ስራ መጀመር ዘመናዊ አሰራሮችን መከተል ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

    የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአሁን ሰዓት 1276 አገልግሎት መስጪያ ጣቢያ እና 2770 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 165/2001 ዓ.ም መሰረት በቦርድ የሚተዳደር መንግስታዊ የልማት ድርጅት ሆኗል፡፡

    ድርጅቱ በ125ኛ ዓመቱን አስመልክቶ በዓሉን ለማክበር የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ነድፎ እየተንቀሣቀሰ ይገኛል፡፡

 ደንበኞች የሚሰጡትን ሀሳብ በአግባቡ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ደርጅት በትግራይ ክልል ከሚገኙ ደንበኞቹ ጋር ውይይት አደረገ፡፡ በየጊዜው ከደንበኞች የሚሰጠውን ሀሳብ በመቀበልም ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
ውይይቱ ህዳር 20 ቀን 2011ዓ.ም በመቀለ ከተማ በዘማሪያስ ሆቴል ከተለያዩ ከተሞች የተወጣጡ ደንበኞች በተገኙበት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ቺፍ ኦፊሰር ወ/ሮ ዝይን ገድሉ ከዚህ ቀደም በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ፣ እንዲሁም የ2011 በጀት ዓመት ድርጅቱ ለማከናወን ያቀዳቸውን ተግባራት አቅርበዋል፡፡ የቀረበው ምላሽም በትክክል መተግበሩን ሀሳባቸውን በመስጠት ተናግረዋል፡፡
ደንበኞችም በተነሱት ጉዳዮች ላይ እና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከተነሱት ሀሳቦችም የትራንስፖርት ድርጅቶችን ሚና ፣ መልዕክት አረካከብን ፣የአዲግራት እና የኮረም ፖስታቤት ህንጻ ግንባታ ፣ ከውጭ የሚላኩ መልዕክቶች እደላ ፣ ከኤርትራ ጋር የፖስታ አገልግሎት ለመጀመር ምን ስራ እየተሰራ እንደሆነ፣የፖስት ባስ ስራን በተመለከተ፣ የፓስፖርት እደላን ማስፋፋትን በተመለከተ፣የታሪፍ ጭማሪን በማስመልክት እና መሰል ሃሣቦችን ተነስተዋል፡፡
በሀሣቦቹም ላይ በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የድርጅቱ ዋና ስራ ስኪያጅ አቶ ግደይ ገብረዮሐንስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የህንጻ ግንባታዎችን በተመለከተ በቀጣዮቹ ወራት መፍትሄ እንደሚሰጣቸው፣ታሪፍን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የበላይ አካላት ጋር በመሆን መጠነኛ ማስተካከያ የተደገና ድርጅቱ ከሚያወጣው ወጪ አንጻር ብዙም እንዳልሆነ፣ከኤርትራ ጋር ያለው የመልዕክት ልውውጥም ከኤርትራ ፖስታ አስተዳደሮች ጋር ውይይት እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡
አቶ ግደይ ሲያጠቃልሉም ለተነሱት ሀሳቦች በሙሉ በጋራ በመወያየት መፍትሄ የሚሰጣቸውን በቅርበት በመነጋገር እንደሚፈታ እንዲሁም ጥያቄዎቹ ለሚለከታቸው የስራ ሂደቶች የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እንደሚበተን እና አፈፃፀሙም ለቀጣዩ መድረክም ምላሽ ተይዞ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ቁጠባ ማህበሩ የብድር ጣሪያውን አሣደገ

የኢትዮጰያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበር አባላት ጠቅላላ ስብሰባ ህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ተደረገ፡፡ የብድር ጣሪውንም አሣደገ ፡፡
በስብሰባው ወቅትም በማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሽመክት ሻውል በስብሰባው የማህበሩ የስራ አፈፃፀም እና የኦዲት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የቁጠባ ማህበሩ የ2010 በጀት ዓመት ካፒታል ብር 26,984,436.30 መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከማህበራት ማደራጃ የመጡት ባለሙያም ማህበሩ ጠንካራ ጐኖች እንዳሉት ገልፀው በግምገማው የታዩ መጠነኛ ጉድለቶችም ከወዲሁ መስተካከል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ወቅቱን የጠበቀ የሂሣብ ምርመራ አለመደረጉ፤ የአባላት መዝገብና የካርድ ምዝገባ የተለያየ በመሆኑ ልዩነቱ ተጣርቶ በአስቸኳይ እንዲስተካከል ሀሣባቸውን አቅርበዋል፡፡

በስብሰባው ተሣታፊ የነበሩ አባላትም ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ከተነሱት ሀሣቦችና ምላሽ ከተሰጠባቸውም በተለይ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር ሼር ግዢ በተመለከተ 2001 ዓ.ም በ500,000.00 ብር የተገዛው አክሲዮን የሚገኘው ዲቪደንድ በሼሩ ላይ እየተደመረ እንዲሄድና የሼር መጠን እንዲያድግ መደረጉና በ2010 ዓ.ም ብር 895,868.96 መድረሱ፣ ክፍፍልንም በተመለከተ የወጣ አባል ኢንቨስትመንት በመሆኑ ሲወጣ ሼሩን ይዞ መውጣቱ እና ዲቪደንዱ የአባላት ብቻ መሆኑ ተገልጿል፤
ከዚህ በተጨማሪ የብድር ጣሪያ መጠኑ 150,000 ብር እንዲሆን እና የቁጠባ መጠኑም 16% እንዲያድግ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የቀድሞ አባላት የሼር መጠን ዝቅያለ በመሆኑ አዲስ ከገቡት ጋር እኩል ለማድረግ ከተቀማጭ ላይ ከኢንቨስትመንት ብር እየተቆረጠ ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አመራሮች ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ወ/ሪት ይፍቱ ስራ መኮንንም የገንዘብ ቁጠባ ማህበሩ ሊቀመንበር አድርጐ መርጧል፡፡

የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ተከበረ

በመላው ሀገሪቱ ለ11ኛ ጊዜ እና በዋናነት በሐረሪ ክልል እየተከበረ ያለው የብ/ብ/ሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች “ህገመንግስታችን፣ ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴ ያችን” በሚል መሪ ቃል በዕለቱ ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በድርጅቱ የስብሰባ አዳራሽ በፓናል ውይይት በድምቀት አከበሩ፡፡

     በዕለቱም የድርጅቱ የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደለ አሰፋ “ህገ መንግስት፣ ብዝሃነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሰነድ ለፓናል ውይይት አቅርበዋል፡፡ 

     በውይይቱም የኢ.ፌዲሪ ህገ መንግስት ዋና ዋና ባህሪያትን፣ ህገ መንግስትና ብዝሃነት፣ የብዝሃነት ጥያቄዎችና አያያዛቸው፣ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ በቀረበው ሰነድ ላይ በስፋት ውይይት ተካሄዶባቸዋል፡፡

    በበዓሉም የሻማ ማብራትና የዳቦ ቆረሳ ስነ-ስርዓት በአቶ ታደለ አሰፋ እና በመሰረታዊ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር ወ/ሮ ዝናሽ አሰፋ የተከናወነ ሲሆን የጥያቄና መልስ ውድድር ስነስርአት ተካሂዶ ለተወዳዳሪዎችም ሽልማት ተበርክቷል፡፡  

2011. Custom text here
Joomla 1.7 templates free by Joomla Template Maker and Free Joomla Templates