Home

ፖስታ ዜናዎች

Print
Category: Postal News
Published Date Written by Administrator

የአለም ፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤ ለማካሄድ ሰነድ ተፈረመ

   የዓለም ፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤን በአዲስ አበባ ለማካሄድ በኢትዮጵያ እና በአለም ፖስታ ህበረት መካከል የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነስርዓት ተካሄደ፡፡

     የፊርማ ስነስርዓቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሸራተን ሆቴል የካቲት 29 ቀን 2010 በተካሄደ ስነስርዓት ተፈጽሟል፡፡

   ከኢትዮጵያ በኩል የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ኤፍራህ አሊ እንዲሁም ከአለም ፖስታ ህብረት በኩል የህብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሁሴን ቢሻር በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

   ክብርት ወ/ሮ ኢፍራህ በስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የአለም ፖስታ ህብረት እና የህብረቱ አባላት ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማስተናገድ ያላትን አቅም፣ እና የፀጥታ ሁኔታ በመረዳት ጉባኤውን እንድታስተናግድ መፍቀዳቸው ኢትዮጵያ በየጊዜው እያሣየች ያለውን ለውጥ የሚያሣይ ነው ብለዋል፡፡

     በልዩ ጉባኤ የአለም ፖስታው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው ሚና በስፋት እንደሚታይ ገልፀዋል፡፡ የውል ስምምነቱም እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ጥረት ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

የዓለም ፖስታ ህብረት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማስተናገድ ላሳየችው ፈጣን ምላሽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

   ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት ፈቃደኛ በመሆኗም ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው የአለም ፖስታ ህብረት እያካሄደ ላለው የሪፎርም ስራ ትልቅ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

   የፖስታው ኢንዱስትሪ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአስገራሚ ፍጥነት እየተቀየረ ይገኛል፤ የኢኮሜርስ ገበያው እና የፋይናንሺያል ሰርቪስ ስራው በመስፋፋቱ በአለም ላይ የሚገኙ የፖስታው አስተዳደሮች አካሄዳቸውን ከዚህ አንፃር እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡ የኢ.ኮሜርስ ገበያው በ2020 የሚኖረው የገበያ ልውውጥ 4 ትሪሊዮን ለማድረስ እቅድ እንደተያዘ ገልፀዋል፡፡ በአፍሪካም የኢኮሜርስ ገበያ ያለ ቢሆንም እስካሁን በደንብ እንዳልሰራበት ተናግረዋል፡፡ የአለም ፖስታ ህብረትም አፍሪካ በዘርፉ ተሣታፊ እንድትሆን ecom@ Africa የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሣቀሰ ይገኛል፡፡

   በአዲስ አበባ በሴፕቴምበር 2018 የሚካሄደውም ልዩ ጉባኤ በህብረቱ ሪፎርም ላይ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ገልፀዋል፡፡

   በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የቀድሞ ቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፣ የመላው አፍሪካ ፖስታ ህብረት ዋና ፀሐፊ አቶ የኑስ ጅብሪን፣ ከአለም ፖስታ ህብረት የመጡ ቴክኒካል ኮሚቴዎች፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት የማኔጅመንት አባላት የድርጅቱ የሰራተኞች ማህበር አመራር እና የተለያዩ የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የህዝብ ክንፍ መድረኩ አገልግሎቱን እንዲያሻሽል እንደረዳው ተገለፀ

የህዝብ ከንፍ መድረኩ በየጊዜው መካሄዱና ፣ ለተነሱ ጥያቄዎችም መፍትሄዎችን ድርጅቱ መስጠት መቻሉ አገልግሎቱን እንዲያሻሽል እና መልካም አስተዳደሩን አንዲያጠናክር እንደረዳው ተገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጀት ከደንበኞችና ከህዝብ ክንፍ አካላት ጋር በተለያዩ ከተሞች መድረክ በመፍጠር ውይይት እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን የዚህ ቀጣይ መርሀግብር የሆነው የሀዋሳ ከተማ የህዝብ ክንፍ ውይይት መጋቢት 20 ቀን 2010ዓ.ም. በሴንትራል ሆቴል ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ከ120 በላይ የሀዋሳ ዞን ፣ የሻሸመኔ ዞን ፣ የአርባምንጭ ዞን እና የባሌ ዞን ደንበኞች እና የህዝብ ከንፍ አካለት ተገኝተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ቺፍ ኦፊሰር ወ/ሮ ዝይን ገድሉ ከዚህ ቀደም በመድረ ኩ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ፣ እንዲሁም የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ክንውን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ደንበኞችም በተነሱት ጉዳዮች ላይ እና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከተነሱት ሀሳቦችም የገጠር የኮሙኒኬሽን ማዕከላትን ፣ የጋዜጣ ስርጭት እና ጥንቃቄን፣ የአገልግሎት መስጪያ ጣቢያ ዎችን፣ ግንባታዎችን፣ ህገወጥ አመላላሾችን፣ የመልዕ ክት መዘግየትን በተመለ ከተ እና መሰል ሃሣቦችን ተነስተዋል፡፡ በሀሣቦቹም ላይ በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩት የገጠር ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማዕከላት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት ጎንደሬ እንዲሁም የዞን አመራሮች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

       ወ/ሮ ዝይን ሲያጠቃልሉም በጋራ በመወያየት መፍትሄ የሚሰጣቸውን በቅርበት በመነጋገር እንደሚፈቱ እንዲሁም ሌሎች የተነሱ ሀሳቦችም በሚመለከታቸው የስራ ሂደቶች የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ወደስራ እንደሚለወጥ እና አፈፃፀሙም ለቀጣዩ መድረክ ምላሽ ተይዞ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ተከበረ

በአገራችን 42ኛው የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን የተከበረው መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በኒያ ፋውንዴሽን የኦቲዝም ማዕከል ሲሆን የድርጅቱ ሰራተኞች የበዓሉ ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ107ኛ እንዲሁም በአገራችን ለ42ኛ ጊዜ የተከበረው የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የዘንድሮ መሪ ቃል “በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን” የሚል ነው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የስርዓተ ፆታ እና የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ሜይንስትሪሚንግ የስራ ሂደት ባለቤት ወ/ሮ እታገኝ ተካልኝ እንደተናገሩት የሴቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እኩልነትን ለማቀናጀት የተከፋለ መስዋዕት በታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቁመው በአገራችን በየደረጃው በሚካሄደው ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶች ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመንግስት በተሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

በዕለቱም በኒያ ፋውንዴሽን የኦቲዝም ማዕከል ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በኦቲዝም ለተጋለጡ ወገኖች ስለሚደረገው እንክብካቤ በፋውንዴሽኑ ኃላፊዎች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት ውይይት ተደርጓል፡፡

   ድርጅቱ የማህበራዊ ግዴታውን ለመወጣት በየአመቱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በመለየት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በዕለቱም ለኒያ ፋውንዴሽን የኦቲዝም ማዕከል ሃምሳ ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ደንበኛ ተኮር አገልግሎት አሰጣጡ ተጠናክሮ ቀጥሏል

     የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በፈጣን መልዕክት፣ በጥቅል፣ በደብዳቤ፣ በፋይናንሻል ቢዝነስ እና በፊላቴሊ በሚሰጣቸው የአገልግሎት ዘርፎች ተደራሽነቱን የበለጠ በማስፋት እየሰራ መሆኑን ከማርኬቲንግና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የስራ ሂደት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

   የሥራ ሂደቱ ለባህር ትራንዚት ድርጅት እና ለቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ በፈጣን መልዕክት አገልግሎት/ኢ.ኤም.ኤስ/ ወደ ተለያዩ የውጪ ሀገራት የሚላኩ መልዕክቶችን አገልግሎት ለመስጠት የወጣውን ጨረታ ተወዳድሮ በማሸነፍ ስራውን ለመጀመር የውል ስምምነቱ ተከናውኖ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች የተጠናቀቁ መሆኑን የሥራ ሂደቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ በልስቲ እሱባለው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የብርሃን ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ፣ ለሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የቤት ለቤት ቅበላና ዕደላ አገልግሎት ስራ ለመስራት ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን የህብረት ባንክ መልዕክቶች በፈጣን መልዕክት ለማመላለስ ውል ተፈጽሟል፡፡

   ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በደብዳቤ አሰራር የስራ ሂደት የህትመት ውጤቶችን የማመላለስ፣ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የዕለታዊ ደብዳቤዎች ቅበላና ዕደላ አገልግሎት እና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብ 7ኛ ዓመት የምስረታ ክብረበዓልን አስመልክቶ የታተመውን የገቢ ማሳባሰብያ ቲሸርት ሽያጭና ስርጭት ስራ በፋይናንሻል ቢዝነስ የሥራ ሂደት በኩል በመስራት ተቋማት በዋና ስራቸው ላይ እንዲያተኩሩ እና የመልዕክት ዝውውሩን ስራ ድርጅቱ ለዚሁ ዓላማ ሥኬታማነት በተደራጀ ሁኔታ በውጤታማነት የማከናወን ሚናውን እየተወጣ ያለ ተቋም መሆኑን ያረጋገጠበት መሆኑም ይታወቃል፡፡

   የስራ ሂደቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን መታሰብያ ቴምብር ህትመት አጠናቅቆ ገበያ ላይ ያዋለ ሲሆን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት 125ኛ ዓመት፣ የኢትዮቴሌኮም እንዲሁም የኢትዮጵያና የሩሲያ ፌዴሬሽን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የተመሰረተበትን 120ኛ የመታሰብያ ቴምብሮች ለማሣተም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰራ መሆኑንም አቶ በልስቲ አስረድተዋል፡፡

   የስራ ሂደቱ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት የአገልግሎት መስጫ ታሪፍ የወቅቱን ገበያ እና የተገልጋዮችን አቅም ባማከለ መልኩ አገልግሎቱን በስፋት ማዳረስ በሚችልበት ሁኔታ የማሻሻያ ስራ በመስራት ተግባር ላይ አውሏል፡፡ እንዲሁም የደብዳቤ አሰራር የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር የአገልግሎት ማሻሻያ ጥናት፣ የፖስታ ሣጥን የኪራይ ማሻሻያ ጥናትና የጥቅል መልዕክት አገልግሎት የሀገር ውስጥ ዋጋ ማሻሻያ ጥናቶች በስራ ሂደቱ እየተገባደደ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

104ኛ ዙር የፖስታ ዕውቀትና የሂሳብ ስራ ስልጠና ተሰጠ

     104ኛ ዙር መሰረታዊ የፖስታ ዕውቀትና የሂሣብ ስራ ኮርስ ስልጠና የተሰጠው ከጥር 28 እስከ መጋቢት 25/2010 ዓ.ም ለሁለት ወራት ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ ከ18 ዞን ፖ/ቤቶች የተወጣጡ 19 ወንድ እና 28 ሴት በአጠቃ ላይ 47 የድርጅቱ ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋ ል፡፡

በስልጠናው ወቅት ስለ ደብዳቤ አሰራር፣ ጥቅል፣ ፋይናንሻል ቢዝነስ፣ የቤት ለቤት ቅበላና ዕደላ፣ የኢ.ኤም.ኤስ፣ የሲምና ቫውቸር ካርድ ማርኬቲንግ አሰራር እንዲሁም የሂሳብ ስራና ሪፖርት አቀራረብ በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት እንደተሰጣቸው የትምህርት ክፍል ቡድን መሪዋ ወ/ሮ አመለወርቅ አብርሃ አስታውቀዋል፡፡

   በስልጠናው ወቅት ሰልጣኞች ሰፋ ያለ ውይይት እና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ፈተና የወሰዱ ሲሆን በተለያዩ የስራ ክፍሎች በመዘዋወር የተግባር ዕውቀት ቀስመዋል፡፡ በስልጠናው ማብቂያ ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደለ አሰፋ እንደተናገሩት ድርጅቱ በየአመቱ ከፍተኛ ወጪ በመመደብ እንዲህ ዓይነት ስልጠና የሚሰጠው ሰራተኞች ድርጅቱ የሚያወጣቸውን ዕቅዶችና ዋና ዋና ተግባራትን በመለየት በተሰማራበት የበኩሉን እንዲወጣ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡ ተቋሙ ባለፉት አስር ዓመታት ዘርፈ ብዙ ለውጦችን እያስመዘገበ መምጣቱን ጠቁመው ለተሻለ ስኬት ሁላችን በተሰማራንበት መረባረብ አለብን የሚል መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

   በምረቃው ስነ - ስርዓት ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ከ1 እስከ 3 ለወጡትም የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

 

 

2011. Custom text here
Joomla 1.7 templates free by Joomla Template Maker and Free Joomla Templates