Home

ፖስታ ዜናዎች

Print
Category: Postal News
Published Date Written by Administrator

የሰራተኞች

ስብሰባ ተካሄደ

     አጠቃላይ የሰራተኞች ስብሰባ ተካሄደ፡፡ ውይይቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሰራተኞች ጋር ጥቅምት 7 እና 8/2013 ዓ.ም በራስ ሆቴል ተካሂዷል፡፡

   ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ መላውን የድርጅቱ ሰራተኛን መሰብሰብ ባለመቻሉ በከተማው ከሚገኙ ግማሽ ሰራተኞች ጋር በሁለት ምድብ በመክፈል ለግማሽ ቀን ውይይቱ ተደርጓል፡፡

     እንደውይይት መነሻም የድርጅቱ የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት በድርጅቱ የእቅድ እና የለውጥ ስራዎች ዲፖርትመንት ቺፍ ኦፊሰር ወ/ት ዘቢደር ታምሩ ቀርቧል፡፡

     ሰራተኞችም አጠቃላይ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን፤ ካነሷቸው ጥያቄዎች ውስጥም አደረጃጀት እና ምደባን ጥቅማጥቅሞችን በድርጅቱ ስላሉ ብልሹ አሰራሮች እና ለውጦች፣ ስለአገልግሎት አሰጣጥ፣ ስለ አገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች ወዘተ የተመለከቱትን አንስተዋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሀና አርአያ ስላሴ ከሰራተኛው ጋር እስካሁን ሰፋ ባለመድረክ ተገናኝቶ መወያየት ያልተቻለው በኮቪድ 19 ምክንያት መሆኑን ገልፀው በተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየት ላይ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል በርካታ ጥያቄዎች በአካል እና በደብዳቤም ከሰራተኛው እንደቀረበላቸው ገልፀው ያሉትን ብልሹ አሰራሮች ለማስተካከል እና ለመለወጥ ጥረት መደረጉን ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱን ወደተሻለ ደረጃ መድረስ የአሰራር፣       የአደረጃጀት ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

     በኦፕሬሽን ዘርፍ ለተነሱ ጥያቄዎች የድርጅቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ተጠባባቂ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በዛብህ አስፋው ምላሽ የሰጡ ሲሆን በሀብት እና በሰው ሀይል ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ደግሞ የሀብት አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አስማረ ይገዙ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወ/ሮ ሀናም በማጠቃለያው ለድርጅቱ ጠንካራ አቅም ለመፍጠር በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

                                       ከደንበኞች ጋር ውይይት ተካሄደ

     የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ደንበኞች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

ውይይቱ ላይም ጥቅምት 10 ቀን በዋሽንግተን ሆቴል የተካሄደ ሲሆን የኢ.ኤም.ኤስ፣ የጥቅል፣ የደብዳቤ፣ የቤት ለቤት፣ የፊላቴሊ፣ የፖስትፋይናንስ፣ የፖስት ባስ እና የፖስታ መደብር ደንበኞች ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በድርጅቱ የኮሙኒኬሽን እና ዓለም አቀፍ ግኝኙነት ቺፍ ኦፊሰር ወ/ሮ ዝይን ገድሉ አማካኝነት የድርጅቱ የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቧል፡፡ ደንበኞቹም በእቅዱ እና በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ በርካታ ግብዓትን ሰጥተዋል፡፡

     ስለመልዕክቶች መዘግየት እና መጥፋት፣ ስለሰራተኞች ስነ ምግባር፣ ስለአገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች ሁኔታ፣ ስለአገልግሎት አሰጣጥ፣ ስለክፍያ አሰባሰብ ስለፊላቴሊ፣ ስለፖስት ባስ፣ ስለ ዳህንነት የመሳሰሉት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

     በውይይቱ ወቅትም የዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በዛብህ አስፋውና የዲፓርትመንት ሃላፊዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ክትትል እና መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮችም በዝርዝር ለሚመለከታቸው ዲፓርትመንቶች ተቆጥረው እንደሚሰጡ እና አፈፃፀማቸውም ክትትል እንደሚደረግ ተነግረዋል፡፡

የደም ልገሣ ተካሄደ

   ኮቪድ 19 መከሰት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ያጋጠመውን የደም እጥረት ለመቅረፍ በድርጅቱ የሴቶች እና ወጣቶች ዲፓርትመንት አስተባባሪነት የደም ልገሣ ተካሂዷል፡፡ የዲፓርትመንቱ ቺፍ ኦፊሰር ወ/ሮ እታገኝ ተካልኝ እንደገለፁት ኮቪድ 19 ከተከሰተ በኋላ ያጋጠመውን የደም እጥረት ለማገዝ የድርጅቱ ሰራተኞች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ ለወገን ደራሽ ወገን በሚል መርሃ ግብር ሰራተኞችን በማስተባበር የደም ልገሣ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

     በዚህም መሰረት በየሶስት ወሩ ፕሮግራም በመንደፍ የደም ልገሣ እየተደረገ ሲሆን ቫይረሱ በአገራችን ከተከሰተ በኋላ በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ለሁለተኛ ጊዜ የደም ልገሣ ተካሂዷል፡፡

     በርካታ ሰራተኞችም የደም ልገሣውን የሰጡ ሲሆን ደም በመለገሣቸውም ደስተኛ መሆናቸውን፣ በዚህ መልኩም ሰብአዊ እርዳታ ማካሄድ መቻላቸውም ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ገልፀዋል፡፡

የፖስት ባስ የቢሮ ለውጥ አደረገ                           

ፖስት ባስ ከዚህ ቀደም በኪራይ አገልግሎት ከሚሰጥበት ቢሮ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ገባ፡፡ የአውቶብሶቹ መነሻና መድረሻ ከዚህ ቀደም ለገሀር የነበረ ሲሆን፤ ለዚህም በወር 80‚000.00 ብር (ሰማኒያ ሺ) እየተከፈለ አገልግሎቱን ሲሰጥ ቢቆይም፤ ቦታው ለልማት በመፍረሱ አጠናተራ ከሚገኘው ከሸበሌ ትራንሰፖርት ውስጥ በወር 90‚000.00 ብር (ዘጠና ሺ ብር) ኪራይ እየከፈለ እንዲሁም ለትኬት መቁረጫ ቢሮ 20‚000.00 (ሃያ ሺ) ብር በአጠቃላይ በወር 110‚000.00 (አንድመቶ አስር ሺ) ብር እየተከፈለ የትራንስፖርት አገልገግሎቱን ሲሰጥ እንደነበር ተገልጿል፡፡

አውቶብሶቹ ጥገና የሚደረግላቸው በዋናው ፖስታ ቤት በመሆኑ ቢሮዎቹም በተለያዩ ቦታዎች በመሆናቸው የስራ መጓተትን በመፍጠሩ፤ ሰራተኞችንም በቀላሉ ማግኘት እና ወጪን መቆጠብ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት የቢሮ ለውጥ በማድረግ ወደ ዋናው ፖስታ ቤት መዛወሩን የዲፓርትመንቱ ተ/ሃላፊ አቶ እዝራ ሣህለድንግል ገልፀዋል፡፡

ይህም ዲፓርትመንቱ በወር ለኪራይ የሚከፈለውን ገንዘብ በማስቀረቱ እና ተጨማሪ የኮንትራት ስራዎችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመስራቱ በአሁኑ ወቅት በአንድ ወር ከተያዘለት እቅድ ከ94 ፐርሰንት በላይ ማከናወን መቻሉም ተገልጿል፡፡ 

በርካታ ተወዳዳሪዎች በመኖራቸው እና በአለም ላይ በተከሰተው የኮቪድ 19 ቫይረስ ምክንያት እንደሌሎቹ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ አውቶብሶቹ መስታወታቸው የማይከፈት በመሆኑ እና ለማቀዝቀዣም ተጨማሪ ነዳጅ ወጪ የሚጠይቁ በመሆናቸው እንደልብ ገበያው ውስጥ ለመግባት እና ተመራጭ ለመሆን እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡

የፖስት ባስ የተቋቋመበት ዋና አላማ መልዕክቶችን በአግባቡ እና ደህንነታቸው ተጠብቆ ለማመላለስ ቢሆንም ከላይ መጫን ያለበት ኪሎ ውስን በመሆኑ ምክንያት እንደ አስፈላጊነቱ ተደራሽ መሆን አልቻለም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከሎጂስቲክ ዲፓርትመንት ጋር በመቀናጀት ስራዎችን በማቀላጠፍ እና መልእክቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለማመላለስ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ኮቪድ 19 በሀገራችን ከተከሰተ በኋላም የመጀመሪያውን ጉዞ በኮንትራት ስራ ወደ ክፍለሀገር በ25/02/2013 ጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ውስጥ የፖስት ባስ ዲፖርትመንት በ 2001 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ካሉት አውቶብሶች ውስጥ 12 አውቶቢሶች በስራ ላይ የሚገኙ መሆኑ ታውቃል፡፡  

                                 የአለም ፖስታ ቀን ተከበረ

የዓለም ፖስታ ህብረት የተመሰረተበት 146 ዓመት በመላው ዓለም በሚገኙ የፖስታ አስተዳደሮችMore than mail” ከደብዳቤ በላይ በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል በተለይ በኢትዮትያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ኮረናን በመከላከል የዘመናዊውን ፖስታ እድገት እናፋጥናለንበሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

     የዓለም ፖስታ ቀን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተከበረው በአዲስ አበባ አሮጌው ፖስታ ቤት የቴምብር አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ነው፡፡ አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያዊያን ብቻ የተነደፉ ወጥ የእጅ ስራ የቴምብር ዲዛይኖች ለእይታ በቅተዋል፡፡   gm2

አውደ ርዕዩ ለተከታታይ 7 ቀናት ለፊላቴሊ አፍቃሪያን እና ለስዕል ጥበበብ አፍቃሪያን መጎብኘት እንዲችሉ ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

በዕለቱ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ / ሐና አርአያ ሥላሴ ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት ዘመናዊ የሆነ አሰራርን ለማሳደግ ፣ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በተጠናከረ ሁኔታ ተግባር ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ድርጅቱ በማምጣት ደንበኞችን አርኪ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች እስከ ገጠር ወረዳ በማድረስና ተደራሽነቱን በማረጋገጥ የተጠቃሚዎቹን እርካታ ለመጨመር ከቀድሞ በተሻለ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

የአለም ፖስታ ህብረት ያስቀመጠውን የአገልግሎት ደረጃ ለማሟላት ሲስተሞችን የማስጀመር እና ለሰራተኞች ስልጠና የመስጠት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ አለም በስፋት እየተጠቀመበት ወዳለው የኢኮሜርስ ስራ ድርጅቱ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ተተኪው ትውልድ በፖስታ ቴምብር እና ከቴምብር ጋር ተያያዙ ስራዎች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ታስቦ የአለም ፖስታ ቀንን በማስመልክት በሀገሪቷ ሰዓሊያን የተነደ የቴምብር ስራዎች ለእይታ እንደበቁም ገልዋል ፡፡

     የዓለም ፖስታ ህብረት ዋና ፀሐፊ ሚስተር ሁሴን ቢሻር በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የፖስታው ኢንዱስትሪ በመገናኛው ዘርፍ ፈር ቀዳጅነቱን በአሁኑ ዘመንም እያሳየ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ አለማችን በአሁን ሰዓትእያስተናገደችው የምትገኘው የኮቪድ 19 ወረሽኝ አሁንም ፖስታ መተኪያ የሌለው የመገናኛ ዘዴ መሆኑን ማሳየቱን ገልዋል፡፡ በተለያዩ አለማት የአየር መጓጓዣዎች ዝግ በሆነበት ወቅት የፖስታው ኢንዱስ ከመልዕክት ማመላለሱ በተጨማሪ የተለያዩ የትራስፖርት አማራጮችን በመጠቀም በጠንካራ ሰራተኞቹ ግንባር ቀደም ተሰላፊነት በመሆን በየቤቱ ተቀምጦ ለነበረው ዜጋው ቁሳቁሶ መድሀኒቶችን፣ የመከላከያ ቁሶችን፣ የምግብ ውጤቶችን እና መሰል ጉዳዮችን አድርሷል፡፡ በዚህም አሁንም ግንባር ተሳታፊነቱን በመቀጠል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የፖስታው ዘርፍ ባለፈባቸው ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን በድል አድራጊነት በመወጣት አገልግሎቱን ማዘመን ችሏል፡፡ አሁንም በርካታ የፈጠራ ተግባራት በወረርሽኙ እንደታዩ እና ጠንካራ የፖስታ አስተዳደሮችም አጋጣሚውን በመጠቀም የበርካታ አገልግሎቶችና የፈጠራ ባለቤቶችም ሆነዋል፡፡

ከጥንት ጀምሮ ጦርነቶች፣ ወረርሽኞች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች መሰናክል ቢሆኑብንም ምንጊዜም ከመልዕክት አድራሽነታችን የሚገታን የለም በማለት ጠቅሰዋል፡፡

   በዕለቱ ፊላቴሊስቶች፣ ሰዓሊያን፣ የኤስ ኦ ኤስ ህፃናት መንደር ልጆች እና የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የፐርፎርማንስ እና ኦዲት ስልጠና ተሰጠ

     በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ትምህርት ክፍል የፐርፎርማን እና ፋይናይሻል ኦዲት ስልጠና ከመስከረም 4 እስከ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም ብዛታቸው አስር ለሆነ የድርጅቱ ሰራተኞች ተሰጥቷል፡፡

     ስልጠናው ሁለት ዘርፎችን ያካተተ ሲሆን አንደኛው ዘርፍ በፐርፎርማንስ ላይ ያተኮረ ነው፤ በውስጡም የፐርፎርማንስ ርዕሰ ጉዳዩን፣ አላማውን፣ አስፈላጊነቱን እና ቅደም ተከተሉን በዝርዝር ተካቷል፡፡

   ይህ ስልጠና የአንድን ድርጅት የእድገት ደረጃ ለማሳየት እና የድርጅቱ ስራ በሚከናወንበት ጊዜ ቅድመ ሁኔታውን እና አሁን የሚገኝበትን ደረጃ ለማነፃፀር ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡

     በሁለተኛው ዘርፍ ስልጠናው ውስጥ የተካተተው የፋይናይሻል ኦዲት አስፈላጊነት፣ የኦዲት ዐይነቶችና የኦዲት መርሆዎች ሲሆን የዚህ ስልጠና ዓላማም በድርጅቱ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት ክፍል እየተደራጀ ነው

     አንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም የደንበኞቹን ፍላጐት ለማርካት ማከናወን ከሚገባቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ የደንበኞች አገልግሎቱ የተጠናከረ እንዲሆን መስራት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትም ከመልዕክት መላክ እና መቀበል ሂደት ጋር በተያያዘ ደንበኞች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡

       በዚህም መሰረት የደንበኞች አገልግሎት የተጠናከረ እንዲሆን በርካታ ማሻሻያዎች ተግባር ላይ ውለዋል፡፡ በቢሮ አደረጃጀቱ ከዚህ ቀደም ተበታትነው የነበሩ የኢ.ኤም.ኤስ፣ የጥቅል እና የደብዳቤ መረጃ መስጪያ ቢሮዎች በአንድ አደረጃጀት ሥር እንዲሆኑ፣ እንዲሁም በአንድ ቢሮ ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

       የሰው ሀይል አደረጃጀቱም እንዲሟላ የተደረገ ሲሆን ደንበኞችም ያለውጣ ውረድ ጥያቄዎቻቸውን በአንድ መስኮት የሚያቀርቡበትን አሰራር መፍጠር ተችሏል፡፡ ከቢሮ አቀማመጥ (ከቢሮ አደረጃጀት) ያደረገው ለውጥም ለደንበኞች እና ለሰራተኞች አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

     በስራም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ተገልጿል፡፡ ተቋርጦ የነበረው የመረጃ አገልግሎት ዴስክም ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ ሀገር ውስጥም ሆነ ወደውጪ የሚላኩ መልዕክቶች ላይ የተለያዩ ችግሮች በሚፈጠሩ ጊዜ የተፈጠረውን ችግር መፍታት እና ዳግመኛ እንዳይከሰት ለማድረግ ጥረት እየተደረገም ይገኛል፡፡

     በአለማችን ላይ የኮረና ቫይረስ በመከሰቱ ምክንያት የተወሰኑ ሀገራት ወደ ሀገራቸው መልዕክቶች እንዳይገቡ እገዳ በማድረጋቸው የተፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት እገዳውን በማንሳታቸው የመልዕክቶች መዘግየት መቀነሱ ተጠቅሷል፡፡  

     ከዚህም በተጨማሪ ከደንበኞች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ጥብቅ ክትትል በማድረግ መልስ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Custom Declaration System (CDS)ስልጠና ተሰጠ

የዓለም ፖስታ ህብረት ከጉሙሩክ ሥራ ጋር በተያያዘ ስራውን የተቀላጠፈ ማድረግ ይቻል ዘንድ የተለያዩ ኤሌክትሮኒካል የአሰራር ዘዴዎችን ቀይሶ በመንቀሣቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ፖስታ አስተዳደሮች ከጃኑዋሪ 1/2021 ጀምሮ መሰል ሥራዎችን ለመስራት የሚያስችለው ቅድሚያ የሚላከው የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ግዴታ እንደሆነ እያሣወቁ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመተግበር ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን አሰራር ለመከተል ስራዎች መሰራት ጀምረዋል፡፡

     በዚህም መሰረት በዓለም ፖስታ ህብረት አሰልጣኝነት Custom Declaration System ስልጠና በኦን ላይን ተሰጥቷል፡፡

     ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከኢ.ኤም.ኤስ፣ ከጥቅል እና ከደብዳቤ ዲፓርትመንት የተወጣጡ 20 የስራ ሃላፊዎች እና ማናጀሮች የአሰልጣኞች ስልጠናውን ተከታትለዋል፡፡

   ከዚህም በተጨማሪ ለስራው ቅርበት ያላቸው በካውንተር እና በመልዕክት ክፍል ውስጥ የሚገኙ 68 የድርጅቱ ሰራተኞች በ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ስልጠናውን ተከታትለዋል፡፡

   የስልጠናው ዋና አላማ ከ2021 ጀምሮ Custom Declaration System በአለም አቀፍ ደረጃ መተግበር ግዴታ በመሆኑ ምክንያት ሰራተኞችን እውቀት ለማስጨበጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

   ሲስተሙም ፖስታ አስተዳደሮች ወደሀገራቸው የሚላኩ ጥቅል መልዕክቶች ቅድሚያ የጉሙሩክ ዴክሌራሲዮን እንዲደርሣቸው ስለሚያደርግ ወደ ተቀባይ ሀገር መግባት የተከላከሉ እና ለደህንነቱ አስጊ የሆኑ በቅድሚያ መለየት ሥለሚያስችል እንዲሁም መልዕክቱ ከመግባቱ በፊት ቅድሚያ ዴክላራሲዮን ተሰርቶ ስለሚጠብቅ ለደንበኞችን የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡           

በተለያየ ምክንያት ጥፋት ያጠፉ ሰራተኞች አስተዳደራዊ እርምጃ ተወሰደባቸው

     የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተለያዩ ጥፋቶችን በፈጸሙ 22 ሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ወሰደ፡፡

ከድርጅቱ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በተገኘው መረጃ መሰረት በድርጅቱ ህብረት ስምምነት ሰነድ እና በሀገሪቱ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት እርምጃ መወሰዱ ታውቋል፡፡

አዲስ የመጣው አመራር ባደረገው ዳሰሳ መሰረት በርካታ ሰራተኞች ጥፋት አጥፍተው በድርጅቱ መመሪያ መሰረት መሰናበት ቢገባቸውም ደመወዝ እየበሉ ይገኙ እንደነበር አቶ አስማረ ይገዙ ገልፀዋል፡፡

በዚህም መሰረት 22 ሰራተኞች ከድርጅቱ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ገንዘብ ያጎደሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በድርጅቱ አሰሪና ሰራተኛ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንድ ሰራተኛ ከ15,000 ብር በላይ ያጎደለ እንዲባረር የሚያዝ በመሆኑ የገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸው ሰራተኞች እንዲሰናበቱ ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ሰራተኞችም በአጠቃላይ ከ15.4 ሚሊዮን ብር በላይ አጉድለዋል፡፡

ከተሰናበቱት ሰራተኞች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደግሞ በዲሲፕሊን ምክንያት የተሰናበቱት ሲሆን በራሳቸው ፈቃድ ከስራ በመቅረት፣ እረፍት ወጥተው በዚያው ሳይመለሱ በመቅረት የደንበኛ መስተንግዶ ላይ ችገር የፈጠሩ እና በተለያዩ ምክንያቶች የተሰናበቱ መሆናቸው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሁለት የስራ መሪዎች ድርጅቱ እና መንግስት የጣለባቸውን ሀላፊነት ወደጎን በመተው እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት ምክንያት ሙስና ሰርተው በመገኘታቸው የሥራ ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

በገንዘብ ጉድለት እና በሙስና ከስራቸው የተሰናበቱ ሰራተኞች በህግ ጉዳያቸው የተያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አቶ አስማረ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም መሰናበት የነበረባቸው እና እስካሁን ሳይሰናበቱ የቀሩ ነገር ግን ጉዳያቸው በይርጋ የሚታገድ ሰራተኞችም በጊዜው አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ አመራር ወደ ስራ ሲመጣ በርካታ የተንጠለጠሉ የዲሲፕሊን ጉዳዮች እንደነበሩ የጠቀሱት ኃላፊው መሰል አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸው ለቀሪው ሰራተኛ እና ለተሰናባቹም ለቀጣይ ህይወቱ ሊሆን እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

           የሥራ ሰዓት ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ድርጅቱ እያከናወነ ያለው የስራ ሰዓት ቁጥጥር ውጤታማ እንደሆነ ተገለጸ፤ቁጥጥሩም ተጠናክሮ ይቀጥላል ፡፡

ድርጅቱ እያሰበ ላለው ስኬት በዋነኛነት የድርጅቱ ሰራተኞች በስራ ገበታቸው መገኘት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

አዲሱ የስራ አመራር በተለያዩ ዲፓርትመንቶች እየተዟዟረ ባደረገው ምልከታ በርካታ ሰራተኞች እንዲሁም የስራ ሃላፊዎች በስራ ገበታቸው ባለመገኘታቸው ምክንያት ስራዎች በአግባቡ እየተሰሩ አለመሆኑን ተገንዝቧል፡፡ በዚህም የስራ ሰዓት ቁጥጥር ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የሰዓት ፊርማ ቁጥጥሩ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡

አንድ ሰራተኛ በቀን 8፡00 ሰዓት በመስራት ክፍያ ሊከፈለው የሚገባ መሆኑን የድርጅቱ አሰሪና ሰራተኛ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ያስቀመጠ ቢሆንም እያንዳንዱ ሰራተኛ ስራውን አክብሮ በተቀመጠለት የስራ ሰዓት በአግባቡ እየሰራ አለመሆኑ በመታወቁ ምክንያት የስራ ሰዓት ቁጥጥሩ ተጀምሯል፡፡

ቁጥጥሩ ከተጀመረ በኋላ ሰራተኞች በጠዋት በስራ ቦታቸው ላይ እንዲሁም የመውጫ ሰዓት ጠብቀው ሲወጡ ታይተዋል፡፡ የድርጅቱ የመጀመሪያ ዋና አላማ ሰራኞች በስራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ማድረግ ሲሆን በዚህም ከ85 እስከ 90 ፐርሰንት ውጤት ተገኝቷል፡፡

በስራ ሰዓት በስራ ቦታ መገኘት ድርጅቱ አዲስ ሊፈጥራቸው ካሰባቸው የድርጅቱ ባህሎች ውስጥ አንዱ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የስራ ሰዓቱ ቁጥጥር ለጊዜው በዚሁ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፤ ወደፊት ኢአርፒ ሶፍት ዌር ተግባራዊ ሲሆን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በአሻራ የስራ ሰዓት ቁጥጥሩ እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡

በተያያዘ ዜናም ከሰኞ እስከ አርብ ከስራ ሰዓት ውጪ እና ከሚመለከታቸው በስተቀር ቅዳሜና እሁድ በስራ ቦታ መገኘትንም በተመለከተ የቅርብ አለቃን አሳውቆ ለሚመለከታቸው አካላት የፈቃድ ፎርም በመላክ ወደስራ ገበታ መግባት የሚቻል ሲሆን ከዚያ ውጪ ግን ማንኛውም ሰራተኛ ከስራ ሰዓት ውጪ በቢሮ ውስጥ መገኘት እንደሌለበት መመሪያ ወጥቷል፡፡

ውሳኔው የተላለፈው የድርጀቱን ንብረት ለመጠበቅ ታስቦ ከደህንነት አንፃር የተላለፈ ሲሆን አደጋ ቢደርስ፣ ንብረት ቢጠፋ በእለቱ በስራ ገበታ ላይ የተገኘው ሰራተኛ ሀላፊነት መውሰድ እንዲችል እንዲሁም የድርጅቱ ንብረት እና ገንዘብ እንዳይባክን ለመቆጣጠር ታስቦ ተግባር ላይ የዋለ መመሪያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

       ድርጅቱ ኮቪድ 19 ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ቀጥሏል

የአለም ፖስታ ህብረት በእርዳታ የላከው ማስክ ድርጅቱ ተረክቧል፡፡ የዓለም ፖስታ ህብርት በህብረቱ የልማት ትብብር ፕሮጀከት አማካኝነት ለ37 በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት እርዳታውን ለግሷል፡፡

በቀጣይም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ ቁሶችን አስመልክቶ ከየሀገራቱ ፖስታ አስተዳደሮች መረጃ ከወሰደ በኋላ ማስክ፣ ሳኒታይዘር፣ እና ጓንት ለመላክ ቃል ገብቷል፡፡

ህብረቱ ለመለገስ ቃል ከተገባው 135,000 የፊት መሸፈኛ ማስክ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 32,000 ማስክ ተረክቧል፡፡

የዓለም ፖስታ ህብረት ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት የፖስታው ሰራተኞች በኮቪድ 19 ወረርሸኝ ወቅት ከፊት መስመር ሆነው ህብረተሰቡን እያገለገሉ እንደሚገኙና ቅድሚያ ተጋላጭ ከሚሆኑት ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ማስክ በመጀመሪያው ዙር ለ37 ሀገራት የተሰራጨ ሲሆን፤ ወጪ የተደረገው ከህብረቱ የልማት ትብብር በጀት እንዲሁም ከቻይና፣ ከፈረንሳይ፣ከጃፓን እና ከሲውዘርላንድ ሀገራት በተገኘ ድጋፍ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የፕሮጀክት ቢሮም ግዢውን እና የሎጂስቲኩን ስራ አከናውኗል፡፡

ከዓለም ፖስታ ህብረት የተገኘውም ማስክ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የድርጅቱ ሰራተኞች ተሰራጭቷል፡፡

   የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከኮቪድ 19 ወረርሽን ጋር በተያያዘ ሰራተኞች ለቫይረሱ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የተለያዩ ትምህርታዊ መረጃዎችን ሰራተኛው እንዲያውቀው ፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎችን፣ሳኒታይዘር እንዲሁም አልኮል እና የእጅ መታጠቢያዎች በየአገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች በማዘጋጀት የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህንንም በተጠናከረ መልኩ እና በዘላቂነት ለመስራት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የንብረት ማስወገድ ስራ ተከናወነ

   በየኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በዋናው መስሪያ ቤት አገልግሎታቸው የተጠናቀቁ ቁሣቁሶች እንዲወገድ ተደረገ፡፡ በልየታውም ተበታትነው የነበሩ ንብረቶች፣ የተቆራረጡ ብረቶች ፣የመኪና ጐማዎች እና እንጨቶች ተገኝተዋል፡፡

     በግቢው ውስጥ የንብረት ማስወገዱ ስራ ድርጅቱን ከማስዋብ ስራ ጋር የተገናኘ ነው፡፡

     የድርጅቱን የማያስፈልጉ ንብረቶች ለይቶ እና በመልክ በመልክ በማስቀመጥ መወገድ ያለባቸው እንዲወገዱ፣ በጨረታ መልክ ለሽያጭ የሚቀርቡም እንዲሁ ዝግጅት እንዲደረግባቸው ተደርጓል፡፡

   በንብረት አስተዳደር ሰብሳቢነት በአምስት ኮሚቴዎች በማዋቀር ስራው ተከናውኗል፡፡ አላስፈላጊ ንብረቶችን በማስወገድ የግቢውን ውበት ቅርጽ እንዲይዝ አድርጐታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይላኩ የቀሩ መልዕክቶች ኮሚቴው ባለበት ተወግዷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የማዕድ ማጋራት እያከናወነ ነው

maedየኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኮቪድ 19 ኮረና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ዜጐች የማዕድ ማጋራት እያከናወነ ነው፡፡

     ድርጅቱ በሚገኝበት ክፍለ ከተማ ሥር ለሚገኙ ሀምሣ ዜጐች ለአንድ ወር የሚቆይ የማዕድ ማጋራት በፊንፊኔ አዳራሽ እያከናወነ ይገኛል፡፡

ፕሮግራሙ ከሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ይቆያል፡፡

     ፕሮግራሙን ያስጀመሩት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሀና አርአያሥላሴ እንዳሉት ድርጅቱ በ126 ዓመታት ጉዞው ህብረተሰቡን በተለያየ መልኩ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን ማህበራዊ ሀላፊነቱንም ለመወጣት የተለያዩ ግለሰቦችን እና ተቋማትን በችግሮቻቸው ወቅት ከጐናቸው በመቆም ሲደግፍ ቆይቷል፡፡

     ለአንድ ወር የሚቆየው የማዕድ ማጋራት ሥራም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው ወደፊት በዚህ የማዕድ ማጋራት ላይ ተሣታፊ የሆኑትን እና ሌሎችን በመጨመር ቋሚ በሆነ መንገድ መርዳት የሚቻልበትን መንገድ ከሌሎች አካላት ጋር በመመካከር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

     ከማዕድ ማጋራቱ ባሻገር ለቤታቸው የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች ለማሟላትም እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቱ መሠል ተግባራት እያከናወነ የወገን አለኝታነቱን በማሣየት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ማኔጅመንት እና ሠራተኞች ችግኝ ተከሉ

/ ሃና አርሃያ ስላሴ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ከድርጅቱ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች ጋር በመሆን ችግኝ ተከሉ፡፡

የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ሰኔ 18 ቀን 2012 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ አካባቢ የተከናወነ ሲሆን በመላ ሃገሪቱ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የአምስት ቢልዮን ችግኝ የመትከል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል ነው፡፡

treplanting

የፖስታ ስራው መነቃቃት እያሳየ ነው

     ኮቪድ 19 (ኮሮና ቫይረስ) ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ቀንሶ የነበረው የመልዕክት ትራፊክ በተለይ በኢ.ኤም.ኤስ በኩል ማንሰራራት እየታየበት ይገኛል፡፡

     በመጋቢት እና ሚያዚያ ወር ተቀዛቅዞ የነበረው የኢ.ኤም.ኤስ የመልዕክት ትራፊክ አማራጭ የማመላለሻ መንገዶችን በመፈለግ ስራው በድጋሚ እንዲያሰራራ ተደርጓል፡፡

     ድርጅቱ የራሱን የትራንስፖርት አማራጭ በመጠቀም መልዕክቶችን የማመላለስ ስራ እየሰራ ሲሆን፤ በተለይ ከሃገር ውጪ ለሚሄዱ መልዕክቶች አማራጭ አመላላሽ ድርጅቶችን በመፈለግ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል፡፡

   በተለይ የኢ.ኤም.ኤስ አፈፃፀም በመጋቢት ወር 27%፣ በሚያዚያ ወር 6% ብቻ የነበረ ሲሆን በግንቦት ወር ግን ከፍተኛ መነቃቃት ማሣየቱ ከዲፓርትመንቱ የተገኘው መረጃ ያሣያል፡፡

   ድርጅቱ በፖስታ ባስ በኩልም ወደ ክፍለ ሀገር የሚደረጉ ጉዞዎች በመረጣቸው ምክንያት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከተቋማት ጋር ኮንትራት በመግባት የሰርቪስ አገልግሎት በመስጠት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

   ከዚህ በተጨማሪ በኢኮሜርሱ ዘርፍ አሁን ያለው ሁኔታ መልካም አጋጣሚዎችን እየፈጠረ በመሆኑ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የአብረን እንስራ ጥያቄ ለድርጅቱ እያቀረቡ መሆኑ ከማርኬቲንግ ዲፖርትመንት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አዲስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተመደበ

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አዲስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምደባ ተካሂዷል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ሀና አርአያ ስላሴ ይባላሉ፡፡ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በህግ ከኒው ዮርክ የህግ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ ወ/ሮ ሀና ፖስታ አገልግሎት ድርጀት ከመቀላቀላቸው በፊት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በምክትል ኮሚሽነርነት፣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በከፍተኛ ፖሊሲ ጥናት አጥኚነት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በህግ ፋኩልቲ በህግ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ አዲሷ ዋና ስራ አስፈጻሚ በዋናው መስሪያ ቤት የሚገኙ የስራ ክፍሎችን በመጎብኘት ከሰራተኞች ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡ የዲፓርትመንት ሀላፊዎችንም በተናጠል በመጥራት ስለሚመሩት ዲፓርትመንት ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክተ ያስተላለፉ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለውን የፖስታ ስራ ለማሳደግ አብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

        የአለም ፖስታ ህብረት በካርጎ መልዕክቶችን ለማደል እየሰራ ነው

የዓለም ፖስታ ህብረት በኮቪድ 19 ኮረና ቫይረስ ምክንያት የመንገደኞች በረራ በተለያዩ ሀገራት በመታገዱ ምክንያት በአለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የካርጎ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተጀመረው ዘመቻ መሳተፉን አስታውቋል፡፡ በአለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር መሰረት ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ባለው መረጃ ከ50 በላ የሚሆኑ የአየር መንገዶች በረራቸውነ አቋርጠዋል፡፡ በዚህም ከ160 በላይ አገራት በዚህ ምከንያት ጫና እየደረሰባቸው ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመንገደኞች በረራዎችም እስከ ጁን 30/2020 ተሰርዘዋል፡፡ በፖስታው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ የፖስታ አስተዳደሮች አብዛኛዎቹ የህብረቱ አባል ሀገሮች መልዕክታቸውን የሚያመላልሱት በህዝብ ማመላለሻ አውሮፕላኖች በመሆኑ በረራዎቹ በመታገዳቸው በፖስታው ዘርፍ ከፍተኛ የመልዕክት ትራፊክ መቀነሱ ተገልጿል፡፡ ከአለም ፖስታ ህብረት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የፖስታ አስተዳደሮች የካርጎ ሰርቪስን እንዲጠቀሙ እና ኮቪድ 19 ኮረና ቫይረስን በተያያዘ የሚያስፈልጉ እቃዎችን በማጓጓዝ የመልዕክት ልውውጡን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ የአለም ፖስታ ህብረት በአለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት የተጀመረውን ዘመቻ እንደሚደግፍና ሀገራትም ቢሮክራሲያቸውን በመቀነስ የካርጎ ትራንስፖርት ሰጪዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥረቱን እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡ የካርጎ ስራ ኮቪድ 19ኮረና ቫይረስ ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት ዋነኛ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለአብነትም ሀይወት አዳኝ የሆኑ መድሀኒቶችን የጫኑ የካርጎ አውሮፕላኖች በሀገራት እልህ አስጨራሽ የሆኑ የቢሮክራሲ ገደቦች ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡ እቃ የጫኑ አይሮፕላኖች በፍጥነት ገብተው ማራገፍ የሚችሉበትን አሰራር አገሮች እንዲቀይሱ፣ የሰዓት እላፊዎች እንዲነሱላቸው፣ የአየር ክልል በረራ ክፍያ እና የማቆሚያ ክፍያ እንዲነሳ፣ እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፖስታ አስተዳደሮች ያለገደብ ጭነት የሚጭኑበት ጊዜያዊ መብት ሊሰጧቸው እንደሚገባ ማህበሩ አሳስቧል፡፡

     የጡረታ ክፍያ ሰፋ ባለ ማዕከል ለመክፈል ጥረት እየተደረገ ነው

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከኮቪድ 19 ኮረና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የጡረታ ክፍያ ይከናወንባቸው  የነበሩ ጣቢያዎችሰፋ ወዳለ ቦታ አየቀየረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከማህበራዊ ዋስትና ባለስልጣን ጋር በመተባበር በየክፍያ ጣቢያዎቹ በመሄድ ቦታዎችን የማመቻቸት፣ የመክፈያ እና የወረፋ መጠበቂያ ወንበሮችን የማዘጋጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ በክፍያው ላይ ለሚሳተፉ ሰራተኞችም አስፈላጊው የቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ ማስጨበጫ እና ትምህርት የመስጠት ስራ ተሰጭቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከኢትየጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተወከሉ በጎ ፈቃደኞች  በየክፍያ ጣቢያዎቹ በመገኘት ለአበል ተቀባዮች ትምህርት የመስጠት ስራ፣ በአልኮል እጅ የማጽዳት፣ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ የማገዝ እና  ወረፋ የማስያዝ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከፖስት ፋይናንስ ዲፓርትመንት በተገኘው መረጃ መሰረት  በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የክፍያ ጣቢያዎች በተፈለገው መልኩ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ድርጅቱ ኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል መንግስት ባወጣው መመሪያ መሰረት ሰራተኞች ፕሮግራም በማውጣት በፈረቃ እንዲሰሩ አስፈላጊ የሆኑ የመከላከያ እርምጃዎች በመውሰድ ደንበኞችን እንዲያገለግሉ፣የመገልገያ ቁሳቁሶችን በተገቢው መንገድ እንዲያጸዱ፣  ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ፣ እጅን በየጊዜው በመታጠብ የቫይረሱን ስርጭት እንዲገቱ እየተደረገ ይገኛል፡፡   

 

2011. Custom text here
Joomla 1.7 templates free by Joomla Template Maker and Free Joomla Templates